አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነጠላ ትርክቶችን በመመከት የጋራ ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት የሚሰራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የመገናኛ ብዙሃን እና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ አመራሮች እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሃይሉ አዱኛ፤ በህዝብ ግንኙነት እና መገናኛ ብዙሃን ፎረም መረጃን መሰረት ያደረገ ግንዛቤ በመፍጠር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም የግጭት መነሻ የሆኑ ነጠላ ትርክቶችን በመመከት የጋራ ሀገራዊ ትርክትን በመገንባት፣ ድልን በማጽናት እና የማህረሰቡን እውነት አደባባይ በማውጣት ረገድ ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን እና ህዝብ ግንኙነት አመራሮች እና ባለሙያዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የህዝብ ግንኙነት እና መገናኛ ብዙሃን ፎረም የዘርፉን አጠቃላይ ሥራዎች በመገምገም ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በማረም ቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡