የሀገር ውስጥ ዜና

በአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ የትራፊክ ደህንነት ችግር እየተስተዋለ ነው ተባለ

By Mikias Ayele

March 05, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ በተደረገ የትራፊክ ቁጥጥር ሥራ የትራፊክ ደህንነት ችግር መስተዋሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደዔታ በርኦ ሀሰን እንደገለፁት÷ባለፉት 9 ቀናት በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች በተደረገ ክትትል በአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ በርካታ ጉድለቶች ተገኝተዋል፡፡

በዚህም የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ሁኔታ ሳያሟሉ ቦሎ ያላቸው ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉና ትርፍ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡

አንዳንድ አሽከርካሪዎች ተደራራቢ የትራፊክ ቅጣት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው÷በሕግ አካላት አስፈላጊው የምክርና የእርምት ርምጃ መወሰዱን አንስተዋል፡፡

በቀጣይ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ በዲጂታል ሥርዓት ከማዕከል ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ለመገንባት እየተሰራ ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡