አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተደመሰሰ፣ በታጠፈና በማይታይ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር ሲገለገሉ ተገኝተዋል በተባሉ 1 ሺህ 587 አሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ከየካቲት 16 ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በቀንና በማታ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡
በዚህም ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ የተሽከርካሪ ሰሌዳን በመጠቀም ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ አሽከርካሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተጠራባቸው ነው ብሏል፡፡
955 ተሽከርካሪዎች የፊት ወይም የኋላ ሰሌዳ ሳይኖራቸው እንዲሁም 633 ያህሉ ደግሞ ለዕይታ ግልጽ ያልሆኑና የተለያየ ቀለም የተቀቡ ሰሌዳዎችን ሲጠቀሙ መያዛቸውንም ጠቅሷል፡፡
ደንብ በሚተላለፉ አካላት ላይ እያደረገ ያለውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡