አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተቋቋሙበትን ዋና ዓላማ መዘንጋት እንደሌለባቸው የትምሕርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አሳሰቡ፡፡
ሚኒስትሩ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ ጋር ዛሬ ባደረጉት ውይይት ላይ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል::
የትምሕርት ተቋማቱ በአካባቢ ሳይታጠሩ ለተመሠረቱበት ዓላማ መኖር አለባቸውም ብለዋል፡፡
የሙስና መንሰራፋት፣ ግብረ-ገብነት ማጣት እና ዕውቀት የመቀያየር ባሕል በምሁራን ዘንድ መቀዛቀዙንም አንስተዋል::
እነዚህ ችግሮች ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት የዕውቀት ማዕከል እንዳይሆኑ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ሀገራችን በዘርፈ-ብዙ ችግሮች ውስጥ በመሆኗ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የመፍትሔ ሐሳብ ማመንጨት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት እና የእውነት ማዕከል እንዲሆኑ ትምሕርት ሚኒስቴር የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ተቋማቱ፤ ጥራት ባለው ትምሕርት ትውልድን መቅረጽ እና የማሕበረሰቡን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችሉ ምርምሮችን በማድረግ ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በገላና ተስፋ