የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሆሚቾ ጥይት ፋብሪካን በጎበኙበት ወቅት ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል …

By ዮሐንስ ደርበው

March 06, 2025

👉 በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ጥይቶችን የማምረት ሙከራዎች ቢኖሩም እስከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ድረስ ሀገራችን ከውጭ በማስገባት ላይ ተመስርታ ቆይታለች፡፡

👉 አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ከማምረት አልፎ ወደውጭ የመላክ ዐቅም አሳድጋለች፡፡

👉 ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በመጠኗ፣ በታሪኳ እና በሀብቷ ልክ እራሷን ጠብቃ ለልጆቿ መሸጋገር መቻሏን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

👉 ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ጥይት (መሣሪያዎች) የማምረት ሙከራዎች ነበሩ፤ እንደዚህ ዓይነት ስትራቴጂክ ዐቅሞች ኢትዮጵያ ካልገነባች በሆነ ጊዜ ማንም መጥቶ ጥቃት ሊፈጽምባት ይችላል የሚል ግምገማ ነበር፡፡

👉 በ2014 ጥይት እንገዛ ነበር፤ ይሁን እንጂ 2015 ላይ ፋብሪካውን መትከል ጀምረን አሁን ለምንገኝበት ደረጃ ደርሰናል፡፡

👉 ዛሬ ኢትዮጵያ ክላሽ፣ ብሬን፣ ስናይፐር፣ ዲሽቃ፣ ታንክ፣ ሁሉም ዓይነት መድፎች ከራሷ አልፎ ለገበያ በበቂ ሁኔታ የማቅረብ ዐቅም ገንብታለች፤ ፋብሪካው ዘመናዊ እና በሠዓት በጣም ከፍተኛ የማምረት ዐቅም አለው፡፡

👉 የፋብሪካው አጠቃላይ ግቢ እና የማምረት ዐቅሙ ኢትዮጵያን ይመጥናል፤ ሀገራችን እንደዚህ ዓይነት ዐቅም ሲኖራት ማየት በጣም ደስ ይላል፤ ያኮራል፡፡

👉 ክላሽ እና ስናይፐርን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎችን እናመርታለን፤ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ከመግዛት ወጥተን ለሀገራት ለመሸጥ በመብቃታችን እና ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ይህ ዐቅም ተገንብቶ በማየቴ ከፍተኛ ክብር እና ደስታ ተሰምቶኛል፡፡

👉 ወታደር ነኝ ይገባኛል፤ በውትድርና አካባቢ የሚጎድሉ ነገሮች በኦፕሬሽን ጊዜ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡

👉 አሁን ኢትዮጵያ ሥጋት የለባትም፤ ጭንቅላት ያላቸው ልጆች አሏት፣ ጀግና ወታደሮች አሏት፣ ከግብዓት አንጻርም የነበረባትን ውስንነት ከሞላ ጎደል ፈትታለች፡፡

👉 ልብስ፣ ጫማ፣ ጥይት፣ ክላሽ፣ ስናይፐር ለወታደሩ ከውጭ እናስገባ ነበር፤ አሁን በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን መከላከያ ልብሱን ያመርታል፣ ጫማ አምርቶ የሚያንሰውን ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ይቀበላል፡፡

👉 ኢትዮጵያ ለበርካታ ሀገራት ጥይት ለማቅረብ የሚያስችላትን ስምምነት (ውል) ፈጽማለች፡፡

👉 በሦስት ወራት ብቻ ከ30 ሚሊየን ያላነሰ ዶላር ሽያጭ ፈጽመናል፤ ይህም ማምረት እና መሸጥ ስለቻልን የተገኘ ውጤት ነው፡፡

👉 በወታደራዊ ዐቅም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው፤ በተለይ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ሴክተሮች አንዱ ኢንዱስትሪው ነው፡፡

👉 የመከላከያ ኢንዱስትሪ ብቻ ያመጣው ዕድገት በጣም ተስፋ ሰጭ እና ኢትዮጵያ በእውነትም እያንሠራራች መሆኗን ማሳያ ነው፡፡

👉 የጥይት ፋብሪካው ኢትዮጵያ ከሥጋት ወጥታ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች አምርታ እራሷን ለመከላከል ብሎም ለማሳደግ የሚያስችል ዐቅም እየፈጠረች ነው የሚለውን በደንብ ያሳያል፡፡

👉 ሀገር ሁል ጊዜም ቢሆን ማምረት የሚገባት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱም ምግብ፣ ልብስ እና መድኃኒት ናቸው፡፡ እነዚህን በበቂ ሁኔታ የማታመርት ሀገር ለማንኛውም አደጋ ትጋለጣለች፡፡

👉 በሁሉም መስክ ስመለከት በጣም ችግር የነበረ፤ በቀላሉ ልናሟላቸው የነበረ ነገሮች ምላሽ እያገኙ ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ተስፋ አላት፣ ኢትዮጵያ እያንሠራራች ነው፣ ኢትዮጵያ ጀምራ እየጨረሰች ነው፡፡

👉 በአንድ ዓመት ተኩል እና በሁለት ዓመት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የራስን ፍላጎት ሸፍኖ ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚችል ኢንዱስትሪ ማየት በጣም ትልቅ ክብርና ኩራት ነው፡፡

👉 ለዚህ ሥራ የመከላከያ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኢንዱስትሪው ኃላፊዎች፣ በሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢው ሠራተኞች ከፍተኛ ክብርና ምሥጋና ይባቸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚስፈልጋትን ዐቅም ፈጥረዋል፤ ገዝተው ሳይሆን አምርተው፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚሸጥ ዐቅም ገንብተዋል፡፡ ለዚህም ኩራት እና ክብር ሊሰማቸው ይገባል፤ እኔም በበኩሌ እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ፤ ደስ የሚል ፍሬ ነው ያየነው፡፡

👉 በርቱ ይቀጥል፤ እንዳይቆም፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ስለሚገባት መርካት ሳይሆን ብዙ መጠማት እና መፈለግ ይገባል፤ ሠራተኞች እንዲመራመሩ እንዲሠሩ ይጠበቃል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው