አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የ12ኛ ዙር የስልጠና መርሐ-ግብር በዋቸሞ፣ ጅማ፣ ወራቤ እና ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ተጀምሯል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ፤ በሥነ ምግባር፣ በክኅሎት እና በሥራ ፈጠራ ግንዛቤ የሚያዳብር ስልጠና በመስጠት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዛሬው ዕለትም 3 ሺህ 366 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአራቱም ዩኒቨርሲቲዎች ሥልጠናቸውን መውሰድ መጀመራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
መርሐ-ግብሩ ለሰላም፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለማኅበራዊ ትሥሥር እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ጉልህ ሚና ስላለው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡