የሀገር ውስጥ ዜና

ከነገ ጀምሮ “መለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ የጀማ ወንጌል ስብከት በመስቀል ዐደባባይ ይካሄዳል

By Mikias Ayele

March 07, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነገ እና ከነገ በስቲያ ከቀኑ 7 ሠዓት ጀምሮ በመስቀል ዐደባባይ “መለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ የጀማ ወንጌል ስብከት እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

መርሐ-ግብሩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ከቢሊ ግራሃም የወንጌል ማኅበር ጋር በመተባበር ነው፡፡

የቢሊ ግራሃም የወንጌል ማኅበር ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቄስ ፍራንክሊን ግራሃም መርሐ-ግብሩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ውብና ጠንካራ ሀገር ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ በመምጣታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

መርሐ-ግብሩ የጸሎት፣ የወንጌል ስብከት እና የዝማሬ ፕሮግራምን ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ፈጣሪን የምናዳምጥበት፣ ስለ ኢትዮጵያና በምድሪቷ ስለሚኖሩ ሰዎች የምንፀልይበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

ቢሊ ግራሃም የወንጌል ማኅበር በ1952 ዓ.ም በወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም በአዲስ አበባ የወንጌል ስብከት ያከናወኑ ሲሆን፤ በንጉሡ ቤተ-መንግስት ተጋብዘው በዐጼ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ተበርክቶላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ልጃቸው ፍራንክሊን በ2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል ዐደባባይ የሚያከናወኑት የጀማ ወንጌል ስብከት አባታቸው ወንጌልን ከሰበኩ ከ65 ዓመታት በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።

በሰለሞን በየነ እና መሳፍንት እያዩ