የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ማፍረስ እንደማይቻል ማረጋገጥ ተችሏል- አቶ አረጋ ከበደ

By ዮሐንስ ደርበው

March 08, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በተወሰደው ሕግ የማስከበር ርምጃ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ማፍረስ እንደማይቻል ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ገለፁ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልል ተመራጮች ከክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ምክር ቤት መሪዎች ጋር  ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ርዕሰ ሥተዳድሩ፤ በክልሉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋ፡፡

በክልሉ በተከናወነው የሕግ ማስከበር ሥራም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል መናድ እንደማይቻል ማረጋገጥ ተችሏል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የፅንፈኝነት አስተሳሰብ ተሰፋፍቶ መቆየቱን አንስተው፤ በተከሰተው ግጭትም ከፍተኛ የሕይዎት፣ የንብረት፣  የሥነ-ልቦና ጉዳት እና ቀውስ መድረሱን ብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ጠንካራ የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት ቀውሱን መቀልበስ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

ለታጣቂ ኃይሎች የሰላም ጥሪ በማድረግ  በርካታ ኃይሎችን ወደ ሰላም መመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከመከላከያ እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት በሠራው ሕግ የማስከበር ሥራ፤ ጽንፈኛውን ኃይል ማዳከም መቻሉን፣ በዚህም ቡድኑ ወደ ሽፍትነት ለመግባት መገደዱን ተናግረዋል፡፡

አሁንም ወደ ሰላም የሚመጡትን ኃይሎች ተቀብሎ በማሠልጠን እና ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የክልሉ መንግሥት ይሠራል ብለዋል፡፡