የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚሽኑ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳለጥ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለፀ

By Melaku Gedif

March 08, 2025

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳለጥ ለባለሃብቶች የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቢክ እስክርቢቶ ግዙፍ ፋብሪካ ለመገንባት አልሳም ግሩፕ እና የፈረንሳዩ ታዋቂ ኩባንያ ቢክ ዛሬ በስካይላይት ሆቴል ባደረጉት የሁለትዮሽ ስምምነት ሥነ-ስርዓት ላይ ነው፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን ስምምነቱን አወድሰው፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚደግፍ እና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የፖሊሲ እና ሌሎች የማሻሻያ ርምጃዎችን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

መንግስት በተገበራቸው የማሻሻያ ርምጃዎችም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲነቃቃ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በስምምነቱ መሰረት ፋብሪካው በአንድ ዓመት ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ሲሆን÷ ወደስራ ሲገባም ምርቱን ለሀገር ውስጥ ለጎረቤት ሀገራት ገበያ እንደሚያቀርብ ተነግሯል።

በዚህም መሰረት ፋብሪካው በኢትዮጵያ መገንባቱ በስራ እድል ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ፣ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የቢክ ኩባንያ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናዎች የስራ ኃላፊዎች በሀገራችን እተከናወኑ ያሉ የትምህርት እና የፈጠራ ተግባራትን ኩባንያቸው የመደገፍ ዓላማ እንዳለው አብራርተዋል።

በሶስና አለማየሁ