አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የኢፈ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን በተለያዩ ክልሎች በማስገንባት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ክልሉ በተለያዩ ክልሎች የኢፈ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ለአገልግሎት እያበቃ ነው፡፡
ይህም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡
ትምህርት የአብሮነት መሳሪያ መሆኑን አውስተው÷አንዱ ክልል ያለውን ሃብት ለሌላው የማካፈሉ ተግባር ለትስስር እና ለጋራ ተጠቃሚነት መሰረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል መንግስት ድጋፍ በተለያዩ ክልሎች የተገነቡ የኢፈ ቦሩ ት/ቤቶች የትምህርት ተደራሸነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በፀሐይ ጉሉማ