የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለደቡብ ኮሪያ ቁልፍ አጋር ናት – አምባሳደር ደሴ

By Hailemaryam Tegegn

March 10, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ኮሪያ በአፍሪካ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ለምታደርገው ተሳትፎ ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኗን በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡

ደቡብ ኮሪያ በአፍሪካ ለምታደርገው የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ያላት የጂኦ-ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የመሠረተ-ልማት እና የሰው ኃይል ምቹ ዕድሎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር የንግድ መሥመር ያላት ቅርበት፤ አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በማገናኘት ረገድ ወሳኝ የንግድ ማዕከል እንደሚደርጋት ነው ከኮሪያ ሄራልድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሱት፡፡

የደቡብ ኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ በአምራች ኢንዱስትሪና በግንባታ ዘርፎች ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተሳትፏቸውን ከዚህም በላይ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

ለዚህም የንግድና የኢንቨስትመንት መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚስፍልግ የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተገበረቻቸው ያሉ ማበረታቻዎች አብራርተዋል፡፡

ደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያ በትምህርት፣ ጤና፣ ኢነርጂ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ድጋፍ እያደረገች መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

ሀገሪቱ በዋናነት የማሽነሪ ግብዓቶችን፣ ኤሌክትሮኒክስና ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ስትልከ፤ በአንጻሩ ቡናን ጨምሮ የግብርና ምርቶችን ከኢትዮጵያ ትቀበላለች፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ