አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር በቀል ዕሴቶች ትኩረት ሰጥቶ ለዓለም እንዲተዋወቁ እየሠራ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
72ኛውን የቦረና አባ ገዳ የስልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት አስመልክተው ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያውያን በርካታ ሀገር በቀል ዕሴቶች አሉን ብለዋል፡፡
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ የሚተገበረውን የገዳ ሥርዓት መሪዎች በሰላማዊ መንገድ የሚቀያየሩበት እና የዴሞክራሲ ዕሴቶችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ሀገር በቀል ልምምድም በአግባቡ ማልማት እና መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተመሳሳይ ባህሎችና ዕሴቶችም፤ ለግጭት አፈታት፣ ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ዋና መሰረት ሆነው ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ ለሀገር በቀል ዕሴቶች ትኩረት መስጠቱን አረጋግጠው፤ የገዳ ሥርዓትን ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ለዓለም ለማስተዋወቅ ብሎም ወደ ልማት ለመቀየር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ