የሀገር ውስጥ ዜና

ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

By Melaku Gedif

March 10, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) አዲሱ ሊቀመንበር የኢጋድ የሚኒስትሮች ም/ቤት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት እና በተለያዩ ጊዜያት የቀጣናው ፈተናዎች እንዲፈቱ ያሳዩትን ቁርጠኝነትና ጠንካራ አመራር ሰጪነት አድንቀዋል።

የስልጣን ዘመናቸው ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ዋና ጸሐፊው÷ኢጋድና የአፍሪካ ህብረት በቀጣናውና በአፍሪካ ሰላምን፣ ደህንነትንና ብልጽግናን ለማስፈን የጀመሩትን የጋራ ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ትብብር፣ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽግናን የሚያጠናክር ሥራ እንዲሰሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡