የሀገር ውስጥ ዜና

ሆስፒታሉ በቅርቡ የጨረር ሕክምና ለመጀመር እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

By ዮሐንስ ደርበው

March 11, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ በቅርቡ የጨረር ሕክምና ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ የካንሰር ታማሚዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ሆስፒታሉ፤ የሕክምና ጥራት እና ዐቅም ማሳደግ የሚያስችል የካንሰር ማዕከል እየገነባ ነው፡፡

ማዕከሉ በሀገር ውስጥ የሚሰጡትን ጨምሮ፤ እስከ አሁን በሀገር ውስጥ የማይሰጡ እንደ መቅኔ ንቅለ ተከላ፣ የኒውክሌር ሜዲስን፣ የፔቲ ስካንና ፒቲስካን ሕክምናዎችን ይጀምራል ተብሏል፡፡

በሆስፒታሉ የካንሰር ስፔሻሊስትና የማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር አብዱ አደም እንዳሉት፤ ማዕከሉ አምስት የጨረር ሕክምና ክፍሎች እና 450 አልጋዎች ይኖሩታል፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች፣ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች እና በአንድ ጊዜ ለ50 ታካሚዎች የኬሞ ቴራፒ ሕክምና መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎች አሉት ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተገነባው ማዕከል ቀሪ ሥራ የማሽን ግዢና ገጠማ መሆኑን ገልጸው፤ ደረጃ በደረጃ የሚጀመሩ አገልግሎቶች አሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ለብዙ የካንሰር ታማሚዎች ፈተና የሆነው የጨረር ሕክምና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ገልጸው፤ አሁን ላይ ማሽኑን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን የመግጠም እና የማስተካከል ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ሲገባም፤ የሆስፒታሉንም ሆነ እንደ ሀገር የሕክምና ጥራቱን የሚያሻሽል ዐቅም እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡

በሐይማኖት ኢያሱ እና ዮሐንስ ደርበው