አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከቻይና ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ቺያዎ ሽዩቢን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የሁለቱ ወገኖች ውይይት፤ ድርጅቱ መሰማራት በሚችልባቸው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ማሻሻልና ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ላይ የፀሐይ ኃይል ተደራሽ ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የከርሰምድር ውኃ ፍለጋና የቁፋሮ ሥራዎች ላይ፣ አጠቃላይ የሳኒቴሽንና የፍሳሽ ማጣሪያ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ መወያየታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
በምክክሩ ላይ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል የማመንጨት ዐቅም መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፖሊሲ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
ቺያዎ ሽዩቢን በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ እንዳለውና በቻይናና በአፍሪካ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት እንደሚታወቅ አስገንዝበዋል፡፡