አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፌዴራል ተቋማት የተቋቋሙ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት 111 መድረሳቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ለሠራተኞች ውጤታማነት የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የህጻናት ማቆያ ማዕከል ያላቋቋሙ ተቋማት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ተቋማቱ ወደ ተግባር እንዲገቡም በሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በኩል ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ለሠራተኞች ውጤታማነት፣ ለህፃናት ደህንነትና ለተቋማት የተሻለ አፈጻጸም የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
የህፃናት ማቆያ ማዕከል በተቋማቸው በመደራጀቱ ሥራቸውን በአግባቡ እየከወኑ ስለመሆናቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ የመንግስት ሰራተኞች አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ መመሪያው ከወጣበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ቢደረግም አፈፃፀሙ ግን ወጥ ባለመሆኑን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡
በፌዴራል መንግስት ተቋማት የህፃናት ማቆያ ማዕከል እንዲቋቋም የወጣው መመሪያ ባለመተግበሩ ዛሬም መቸገራቸውን ሴት የመንግስት ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡
በተካልኝ ኃይሉ