የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

By Hailemaryam Tegegn

March 12, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው የሚኒስትሮች ጉባኤ አካል የሆነው የቴክኒክ ባለሙያዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ትግበራ ምሳሌ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን መቻሏን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው በመሰረተ ልማትና በኃይል አቅርቦት ትስስር እያከናወነቻቸው ያሉትን ተግባራት ጠቅሰው፤ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ መፋጠን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ጉባዔው “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤ አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” በሚል መሪ ሃሳብ እስከ መጪው ሰኞ ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ጉባኤው በዋናነት የአፍሪካን የልማት አጀንዳዎች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ሲሆን የዲጂታላይዜሽን፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢነርጂ ጉዳዮች እና የምግብ ዋስትናን እንደሚሸፍንም ተጠቁሟል።

በሰለሞን በየነ