አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ለሕዝቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መሥተዳድሩ፥ በክልሉ ምሥራቃዊ ሲዳማ ዞን በግንባታ ላይ ያሉ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።
ከተጎበኙት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል፤ በቦና ዙሪያ ወረዳ እየተካሄዱ ያሉ የመንገድና ድልድይ ግንባታዎች ይገኙበታል።
በተመሳሳይ አቶ ደስታ በዞኑ ቡራ ወረዳ የውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታን የተመለከቱ ሲሆን፤ ጉብኝቱ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በመገምገም ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚሁ ወቅትም የክልሉ መንግሥት ለሕዝቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጎበኟቸው የመንገድ፣ ድልድይና የውኃ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲጀምሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ምልከታ በሌሎች ወረዳዎችም እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡