አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ የሚገኘው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ በሰፊው ሊሠራበት ይገባል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ሲያከናውናቸው በቆዩ ተግባራት ላይ ከኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ ጋር ጠቃሚ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ክልሉ የበርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ባለቤት በመሆኑ ሃብቶቹን በማስተዋወቅ ረገድ ኮሚሽኑ ጠንካራ ልምድ አካብቷል ብለዋል፡፡
ይህን ልምዱን ለሌሎችም ለማካፈልና ከክልሎችም ጋር ይበልጥ መተሣሠር እንደሚገባም በውይይታችን አንስተናል ነው ያሉት።
ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ የሚገኘው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ በሰፊው ሊሠራበት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ለዚህም ሀገር አቀፍ ትሥሥርን መፍጠርና የጉብኝት ባህልን ይበልጥ ማስፋት ይገባል ብለዋል፡፡