የሀገር ውስጥ ዜና

የትምህርት ተደራሽነትን የማስፋት ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው – የክልሉ ትምህርት ቢሮ

By Hailemaryam Tegegn

March 23, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሀገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ የመጽሐፍና የትምህርት መርጃ መሳሪያ እጥረትን ማቃለል መቻሉን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተቀረጸው “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” ኢንሼቲቭ ህዝቡን በማስተባበር ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ችግር ማቃለል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ታምራት ይገዙ (ዶ/ር) የትምህርት ቤቶች ግንባታን የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፥ የሀገር አቀፉ ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ሽፋንንና ጥራትን በማሳደግ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በዘንድሮው ግማሽ በጀት ዓመት 4 ሺህ ለሚሆኑ መምህራን የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና መሰጠቱን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በክልሉ በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ላይ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡