የሀገር ውስጥ ዜና

ክልሉ የዒድ አልፈጥር እና የፋሲካ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ለ472 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

By ዮሐንስ ደርበው

March 26, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት 1 ሺህ 446ኛውን የዒድ አልፈጥር በዓል እና መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ472 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በወንጀል ጉዳይ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ከሚገኙት ውስጥ ሕጉ የሚጠይቀውን መመዘኛ አሟልተው ለተገኙ በመደበኛ ለ459 ወንዶች፣  እና ለ12 ሴቶች እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ለ1 ሴት የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል፡፡

ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል፤ 471 በሙሉ ይቅርታ ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በክልሉ መንግሥት ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ-ታራሚዎች በማረሚያ ቆይታቸው ወቅት፤ በቂ ትምህርት የተሰጣቸውና በፈፀሙት የወንጀል ድርጊት ተፀፅተው የታነጹ ስለመሆናቸው በየደረጃው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

አንዳንዶቹም እርቅ ስለመፈጸማቸውና የገንዘብ መቀጮ ያለባቸውም ገንዘቡን ስለመክፈላቸው ስለተረጋገጠ ሕብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላችው መጠየቃቸው ተጠቁሟል፡፡

የይቅርታው ተጠቃሚዎች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሲቀላቀሉ፤ በመልካም ሥነ-ምግባራቸው ዓርዓያ በመሆን ሕብረተሰቡን እንዲክሱ ርዕሰ መሥተዳደሩ አሳስበዋል፡፡