የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ትንሣኤ በኢትዮጵያ ማንሠራራት ተጀምሯል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By ዮሐንስ ደርበው

April 19, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ትንሣኤ በኢትዮጵያ ማንሠራራት ተጀምሯል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትንሳኤ በዓል እንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፤ የኢትዮጵያ ጸጋ ለዓለም እየተገለጠ ነው ብለዋል፡፡

የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

እንኳን ለትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ

ትንሣኤ የማሸነፍ በዓል ነው። ራሳችን እስካልተሸነፍን ድረስ ማንም ሊያሸንፈን እንደማይችል እንማርበታለን። ሮማውያንና አይሁድ በክርስቶስ ላይ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ነበር። ፈርደውበታል፤ ገርፈውታል፤ ጎትተውታል፤ ሰቅለውታል፤ ገድለውታል። በመጨረሻም በመቃብር ቀብረው መቃብሩን አትመውታል።

እነዚህ ሁሉ ነገሮች ኢየሱስ ክርስቶስን በመቃብር አሥረው ከትንሣኤ አላስቀሩትም። በትንሣኤ ሌሊት፣ ሞት ታሪክ መቃብርም ተረት ሆነ። ያ ሁሉ ግርግርና ጩኸት ከንቱ ሆነ። ከሞት አጠገብ ሕይወት፣ ከመቃብር አጠገብ ትንሣኤ ተገለጠ።

እውነትን ማን ሊያሸንፋት ይችላል? ፀሐይንስ ማን ሊሸፍናት ይችላል?

አውሎና ወጀቡ የሚያሸንፉት ለመሸነፍ የተዘጋጀውን ነው። ጩኸትና ግርግር የሚያስደነብሩት ለመደንበር የተዘጋጀውን ነው። ወሬና ሐሜት የሚያስደነግጡት ለመደንገጥ የተዘጋጀውን ነው። ለማሸነፍ የወሰኑትን ማንም ምንም አያደርጋቸውም።

የረቡዕን አድማ፣ የኀሙስን ሤራ፣ የዓርብ ጠዋትን የጲላጦስ ፍርድ፣ የዓርብ እኩለ ቀንን ጨለማ፣ የቅዳም ስዑርን የከበደ ጸጥታ – ላየ፣ ሁሉም ነገር ያለቀና የተቆረጠ ይመስል ነበር።

ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ግን ሁሉም ነገር ተገለበጠ። ታሪክ ተለወጠ፤ እውነት ተገለጠ። ሐሰት ደነገጠ። ጠላት ተናወጠ።

የኢትዮጵያ ትንሣኤ በኢትዮጵያ ማንሠራራት ተጀምሯል። ጩኸቱ እያለፈ ነው። ጨለማው እየነጋ ነው። ሤራው እየተበጣጠሰ ነው። ሁሉንም ወደ ኋላዋ እየተወችው ነው። የኢትዮጵያ ጸጋ ለዓለም እየተገለጠ ነው። በጲላጦስ ዐደባባይ በኢትዮጵያ ላይ ሲጮኹ የነበሩ ሁሉ፣ እጃቸውን በአፋቸው ይጭናሉ። ዓይናቸው እያየ ኢትዮጵያ ስትነሣ ያያሉ። ‘የወጉት ያዪታል’ እንዲል።

በድጋሚ መልካም በዓል ይሁንልን።