አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትንሳዔ በዓልን ስናከብር ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላምና እርቅን በማጉላት መሆን አለበት ሲሉ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች አመለከቱ።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገራችን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች በስብራት የተሞሉና ውድቀትን ሲያስተናግዱ የመጡ፣ በነጠላ ስርዓት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ ብለዋል።
ከዚህ አዙሪት ለመዉጣት ትውልዱ በመደመር እሴት ታንፆ በፍቅር ወደ ዘላቂ ብልፅግና እንዲሸጋገር መንግስታችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የጦርነትን ምዕራፍ በመዝጋት ሰላምን በማስፈን የተጀመረዉን ብልጽግና የማሳካት ጉዞ እውን እየሆነ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት አቋም ዴሞክራሲን ማፅናት፣ ሰላምን ማስፈንና ብልፅናን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።
እምነት ሁሉ መልካም የስራ ባህልን የሚያበረታታና ብልፅግናን የሚያጠናክር በመሆኑ መንግስታችን የሃይማኖትን መልካም እሴት ለሀገር ግንባታ በማዋል ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር ስኬታማ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ተባብረን በመስራት ፈተናዎችን አሸንፈን ብልፅግናን እናሳካለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልላችን ሰላምን ለማስፈን የጀመርነዉን ጥረት በፀና መሠረት ላይ ለመትከል የሃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የትንሳዔ በዓል ሲከበር የታረዙትን በማልበስ፣ የተራቡትን በማብላት፣ የታመሙትንም በመጠየቅ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላምና እርቅን በማጉላት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ማዕድ አብሮ በመጋራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በጀመርናቸው ሁሉ አቀፍ የልማት ሥራዎች በትብብርና በቅንጅት በመሥራት ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ ውጤታማ ሥራዎችን በመስራት አዲስ ብስራትን ማብሰር ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለሁላችንም የጋራ የሆነችውን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ባስተማረን ትህትና መሰረት ህዝባዊ ጥቅምን አስቀድመን መክፈል ያለብንን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍለን የህዝባችንን ሰላም በማረጋገጥ የልማትና የብልፅግና ትንሳኤያችንን እናፋጥን ብለዋል።
በመጨረሻም አቅም ያላችሁ የክርስትና እምነት ተከታዮች አቅመ ደካማ ወገኖቻችሁን በመርዳት፤ ጧሪ የሌላቸውን አረጋዊያን በመደገፍ ፤ ያላችሁ ለሌላቸው በማካፈል በዓሉን እንድታከብሩ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በዓሉ የመረዳዳት እሴትን በሚያጎለብት መልኩ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።