አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በዓሉ የሰላም እና የደስታ እንዲሆን በመመኘት÷ የበዓል ወቅት ለኢትዮጵያውያን ጤና፣ ሰላም እና ተስፋን ይዞ እንዲመጣ እምነት አለኝ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም የትንሣኤን በዓል ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በዓሉ የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል።
የበዓሉ ወቅት ደስታ፣ በረከት፣ መልካም ነገር እና ዳግም የመታደስ ስሜት ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የደስታ እና የበረከት እንዲሆን ልባዊ ምኞቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ ኤምባሲ እና ሰራተኞቹ ለመላው ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መልካም የትንሣኤ በዓል እንዲሆን በመመኘት÷ በዓሉ የደስታ እና የበረከት ይሁን ሲልም ገልጿል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን በኢትዮጵያ የትንሣኤ በዓልን ለምታከብሩ በሙሉ መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ በበኩሉ÷ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የደስታ እና የበረከት እንዲሆን ተመኝቷል።
በተመሳሳይ የኔዘርላንድስ፣ ስዊድን፣ አልጄሪያ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ስሪላንካ ኤምባሲዎች ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።