አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራን ስንጀምር በቅድሚያ ትኩረት የሰጠነው እና ያሰብነው “ሰውን” ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ ለሕዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር ያረጋገጥንበት የካዛንቺስ-ሜክሲኮ-ለገሀር-ቸርችል-የእስጢፋኖስ-4 ኪሎ ኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራዎቻችን በዛሬው ዕለት መርቀን ለነዋሪዎቻችን ግልጋሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።
የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራን ስንጀምር በቅድሚያ ትኩረት የሰጠነው እና ያሰብነው “ሰውን” ነው ያሉት ከንቲበዋ÷ ነዋሪዎችን ፍፁም ለመኖር ምቹ ካልሆነ ሁኔታ እና አካባቢዎች በማውጣት ምቹ የመኖሪያ አካባቢን በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
1 ሺህ ሄክታር መሬት በሸፈነው የካዛንቺስ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ 40.9 ኪ/ሜ የአስፋልት መንገድ ዝርጋታ፣ 81.9 ኪ/ሜ የእግረኛ መንገድ ግንባታ፣ 20.7 ኪ/ሜ ሳይክል መስመር፣ 15 የህጻናት መጫዎቻ ቦታዎች፣ 8 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ 16 የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች እና አረንጓዴ ፓርኮች፣ 19 የመጸዳጃ ቤቶች፣105 የንግድ ሱቆች፣ 40 የመኪና ማቆሚያዎች እና ተርሚናሎች ተካትተው መገንባታቸውንም አመላክተዋል።
105 ሱቆችን በመገንባት ከዚህ ቀደም በአካባቢው በልማት ለተነሱ ነጋዴዎች እንዲሁም ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለተመረቁ ሴቶች አስተላልፈናልም ነው ያሉት።
ሀገርን የመገንባት ራዕያችን እውን እንዲሆን በልማት የተነሳችሁ ነዋሪዎቻችን፣ በገንዘብ፣ በጉልበት እንዲሁም ሃብት በማስተባበር ሀገር በጋራ ለማነፅ በቅንነት ከጎናችን ለቆማችሁ ባለሃብቶች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እንዲሁም አመራሮች ሁሉ በከተማ አስተዳደራችን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላደረጉት ድጋፍ እና የቅርብ ክትትል በራሳቸውና በነዋሪዎች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።