አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አ.ማ ከባቡር ጭነት በተጨማሪ የትራንዚት፣ የጉምሩክ አስተላላፊነትና የሎጅስቲክስ ስራዎችን በማቀናጀት የተቀላጠፈ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አ.ማ የጀመረው አዲስ አገልግሎት የንግድና የሎጅስቲክስ ስራዎችን እንደሚያሳልጥ በተቋሙ የግሎባል ሎጅስቲክስ ዳይሬክተር ወ/ሮ ምንተስኖት ዮሃንስ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ አስመጪና ላኪዎች ከአሁን ቀደም ከውጭ ትራንዚተሮች ያገኙ የነበረውን የጉምሩክና የወደብ ዶክመንት አገልግሎት በአንድ ማዕከል ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ የትራንስፖርትና የጉምሩክ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በመስጠት አስመጪና ላኪዎች የሚገጥማቸውን መጉላላት የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው፥ የአገልግሎት ክፍያው ከወደብና ከጉምሩክ ክፍያዎች ውጭ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተገልጋዮች የሎጅስቲክስና አጠቃላይ ሂደቶችን መከታተል የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱንም ወ/ሮ ምንተስኖች ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አ.ማ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚጠይቀውን ዋጋ በተመለከተ በ9546 በመደወል ማወቅ እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ