የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

April 30, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የጎደሏትን መሰረተ ልማቶች በማሟላት ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በትናንትናው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የቡልቡላ ፓርክ እና ከቦሌ ካርጎ እስከ አቃቂ ድልድይ ድረስ የ14 ኪ.ሜ የአረንጓዴ ልማት ስራ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም አዲስ አበባን ስሟን የሚመጥን ውብ ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ተጠንተው እየተገነቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዚህ አካል የሆነው የቦሌ ቡልቡላ ፓርክ የሰርግ ቦታዎች፣ የህፃናት ማጫዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ፋውንቴኖች እና ሌሎች አረንጓዴ ስፍራዎችን አካቶ የያዘ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህም የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲዝናኑ እና መንፈሳቸውን እንዲያድሱ ያደርጋል ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ በተለይም ወጣቶችና ታዳጊዎች በአልባሌ ቦታዎች ከመዋል ይልቅ በፓርኩ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያንፁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ ግንባታ ወቅት የአካባቢው ማህበረሰብ አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው÷ ”ስንተባበር ፕሮጄክቶችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደምንችል አሳየተናል” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን ስሟን የሚመጥን ውብ ከተማ ለማድረግ የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በሂደቱም ተሳትፎ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ