የሀገር ውስጥ ዜና

በቤይሩት ፍንዳታ 1 ኢትዮጵያዊ ሲሞት 9 ጉዳት ደርሶባቸዋል

By Feven Bishaw

August 07, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ1፣2012 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ ሃገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከስራ ውጭ የሆኑ፣ በእስር እና በስደት ላይ የነበሩ 218 ዜጎች ባለፉት 2 ሳምንታት ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  መግለጫ ሰጥተዋል ፡፡

በመግለጫቸው በተለያዩ ሃገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከስራ ውጭ የሆኑ፣ በእስር እና በስደት ላይ የነበሩ 218 ዜጎች ባለፉት 2 ሳምንታት ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በቤሩት በደረሰው የፍንዳታ አደጋ የአንድ ኢትዮጵያዊ ህይወት ሲያልፍ በ9 ኢትዮጵያውያን ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ቃል አቀባዩ  በቤሩት በሚገኙ 3 አካባቢዎች በሚገነው ዜጎች ላይ ጉዳት አልደረሰም ብለዋል።

ሆኖም ከጉዳቱ ስፋት አኳያ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች  ካሉ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የውሃ ሙሌት ደንቧን ማቅረቧን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ድርድሩ ሁለቱ ሃገራት ደንቡን ለመመልከት ቀን ይሰጠን በማለታቸው መቋረጡን አስረድተዋል።

በተለይ በድርድሩ ላይ ከግድቡ ጋር በማይገናኝ መልኩ በዘላቂ የውሃ አጠቃቅም ዙሪያ ከስምምነት እንድረስ በሚል እየተነሳ ያለውን ጥያቄ ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በድርድሩ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን  ዘላቂ አጠቃቀም በተመለከተ በሌላ ድርድር የሚታይ እና ሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት በተካተቱበት ሁኔታ ብቻ ድርድር ይካሄዳል በሚል አቋሟ ጸንታለችም ነው ያሉት፡፡

በተያዘው ቀጠሮ መሰረትም ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ በመጭው ሰኞ  ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላትም አስታውቀዋል፡፡

 

በምስክር ስናፍቅ