አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ ሙከጡሪ ከተማ አቅራቢያ መቼላ ቀበሌ ቄሌምቶ ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ እስከ አሁን የሥድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
ከሟቾች በተጨማሪ በ21 ሰዎች ላይ ከባድ እንዲሁም በሌሎች 17 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታከለ ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
አደጋው የደረሰው ከሙከጡሪ ወደ ጂዳ ሲጓዝ የነበረ በተለምዶ አይሱዚ ተብሎ የሚጠራው ቅጥቅጥ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከለሚ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ከነበረ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨታቸው ነው ብለዋል፡፡
አደጋው 7 ሠዓት 30 ላይ መድረሱን ለፋና ዲጂታል ያረጋገጡት ኃላፊው፤ የአደጋውን ክብደት ጠቅሰው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው