አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) በዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል።
እስካሁን 7 ነጥብ 3 ቢሊየን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መደረጋቸውን ያነሱት እያሱ (ፕ/ር)÷ ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ 40 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ከነዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ለምግብ ዋስትና አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ፍራፍሬዎችና የመኖ ችግኞች እንደሆኑ አመላክተዋል።
እስካሁን ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውን ገልጸው፥ በዘንድሮው ንቅናቄ የሚተከሉት ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲፀድቁ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
በዙፋን ካሳሁን