አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሥጋ ምርት ቻይናን ጨምሮ በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተመራጭ እንዲሆን ለማስቻል ከቻይና ጋር በትብብር የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በደቡብ ደቡብ ትብብር በተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን ያሳደጉት ኢትዮጵያ እና ቻይና የእንሥሣትን ምርታማነትን ለማሣደግ የሚያሥችሉ ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን በትብብር እያከናወኑ እንደሆነ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያን ከፍተኛ የእንሥሣት ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የእንሥሣት ምርት እሴት ሰንሰለት አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆኗል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የእንሥሣት ሀብት ልማት አማካሪ አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በዘርፉ የሁለቱ ሀገራት ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየሠራች በምትገኘው ሥራም የእንሥሣት ሀብቷን በአግባቡ እየተጠቀመች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሊዩ ዋንግ፤ የኢትዮጵያን የሥጋ ምርት ቻይናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተመራጭ ለማድረግ የጀመርናቸው ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የእንሥሣት ሀብት ምርታማነት ላይ ለመስራት ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረው የእንሥሣት ምርት እሴት ሰንሰለት አቅም ግንባታ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ውጤት የታየበት መሆኑን አንስተው፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ዛሬ ይፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰለሞን ይታየው