የሀገር ውስጥ ዜና

በድሬዳዋ የደንጊ በሽታን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው

By Melaku Gedif

May 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የበልግ ዝናብን ተከትሎ የሚከሰተውን የደንጊ በሽታ ለመከላከል የቅድመ መከላከል ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ተሾመ እንደገለጹት÷ ባለፉት ዓመታት የደንጊ በሽታ በአስተዳደሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፡፡

በተያዘው ዓመትም የበልግ ዝናብን ተከትሎ ሥርጭቱን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመላክተዋል፡፡

በተለይም የአጎበር ሥርጭት እና ውሃ የሚያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው÷ የደንጊ በሽታ የሚያሳያቸው ምልክቶች ከወባ ጋር የመሳሰል ባህሪ እንዳላቸው አብራርተዋል።

ሚኒስቴሩ በድሬዳዋ አስተዳደር በቂ የአጎበር ሥርጭት በማከናወን በሽታውን ለመከላከል እየሰራ እንደሚገኝም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም