አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የምክር ቤት አባላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የኦሮሚያ ክልል የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን በተመለከቱበት ወቅት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የፍትህ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑን መገንዘብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ፈጣን እንዲሆን የአመራርና ፈፃሚ አካላት የተቀናጀ ድምር ውጤት ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ችሎቶች መንጸባረቁን ገልጸዋል።
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሁም በዞንና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በአመራርና በፈፃሚዎች ቅንጅት የተመዘገበው ውጤት በሌሎች ክልሎች በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑንም አመልክተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስገነባው ህንፃ የተዘረጋው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ህዝቡ ፈጣን የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።
በክልሉ የፍትህ ተደራሽነቱ በቴክኖሎጂ መመራቱ ተገልጋዮች ሳይንገላቱ፣ ለወጪና ለጊዜ ብክነት ሳይዳረጉ ካሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ክልሉ የዳኝነት ስርዓቱንና አሰራሩን በማሻሻል ረገድ የሰራው ትርጉም ያለው ስራ ተሞክሮ ሊወሰድበት እንደሚችልም አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባስመል፤ በበኩላቸው የህዝቡን አመኔታ ያተረፈ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
መደበኛና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ ሳይገባ በትብብር መስራታቸው አመርቂ ውጤት ለማምጣት ማስቻሉን አንስተዋል።
በፍትህ አገልግሎት ተደራሽነት ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለሌሎች ክልሎች በማጋራት በትብብር እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።