አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለሀገራችን የአገልግሎት አሰጣጥና የመንግሥት አስተዳደር ሪፎርም ወሳኝ ምዕራፍ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና መነሻ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር ዕድገት ለዜጎች በሚሰጥ አገልግሎት እንደሚወሰን ገልጸው፤ ዜጎች ፈጣን አገልግሎት ካላገኙ ከግለሰባዊ እንግልት ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳለው ተናግረዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ዋና ዓላማ የዜጎችን እንግልት የሚያስቀር፣ ከሙስና የጸዳ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት የጀመረውን የአገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ሪፎርም ለማሳለጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በርካታ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በርካታ ሚሊየን ዶላር እንደሚጠይቅ አውስተው፤ ይህን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እውን አድርጋዋለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መሪነት የሌሎች ተቋማትን የቴክኖሎጂ መሃንዲሶች በማሳተፍ ዘመኑን የዋጀ፣ አስተማማኝና ቀልጣፋ የዲጂታል ስርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል።
ማዕከሉን ልዩ የሚያደርገው ሰዎች ሥራን የሚመሩበት ሳይሆን ሥራ ሠራተኛን የሚመራበት መሆኑ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተገልጋይ ካመለከተበት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ያለውን የሥራ ሂደት የሚከታተልና የሚቆጣጠር ዲጂታል ስርዓት መኖሩን ጠቅሰው፤ ሥራ የሚያጓትቱ ፈጻሚዎች በቴክኖሎጂ ሪፖርቱ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በማዕከሉ የተመደቡ ሠራተኞች በብቃት ተመዝነው ያለፉ እንዲሁም ተገልጋይን በክብርና በፍጥነት ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም ያላቸው ናቸው ብለዋል።
መሶብን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋት መታቀዱን ገልጸው፤ እያንዳንዱ ክልል ቢያንስ አንድ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲከፍት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግሥትም በራስ አቅም የለማውን ቴክኖሎጂ ስርዓት እንደሚዘረጋላቸው፤ የአቅም ግንባታና የማማከር አገልግሎትም እንደሚሰጣቸውም አረጋግጠዋል።