የሀገር ውስጥ ዜና

መንግስት በሲኖዶስ ጉባኤ መሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገለጸ

By Abiy Getahun

May 02, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዚህ በፊት አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ መንግሥት ሀገራዊ ተቋማትን ለማጠናከር ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው ብሏል።

ከዚህ በፊት አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን መንግሥት ገልጿል።

ሀገራዊ ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን የላቀ ሚና መንግሥት ስለሚረዳ በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዲፈታ መንግሥት የመሪነቱን ሚና መጫወቱን አስታውሷል።

ቤተ ክርስቲያኗ በሀገር ግንባታ የነበራትንና የሚኖራትን ሚና በመገንዘብ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል ያለው መግለጫው፤ በዚህ አቋሙም ይቀጥላል ብሏል።

ይሄንን ያልተረዱ አንዳንድ አካላት ችግሮችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም እንኳን፤ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኗ እና ለምእመኗ ሲል በሆደ ሰፊነት ለማለፍ ወስኗል በማለት ገልጿል።

ይሄም ከግለሰቦች ችግር ይልቅ የቤተ ክርስቲያኗን አስተዋጽዖ ስለሚመለከት ነው ብሏል።

መንግሥት ችግሩ እንዲፈታ ሲኖዶሱ ያቀረበውን ጥያቄ መቀበሉን ገልጾ፤ በሂደቱም ተቀራርቦ መነጋገር ከሁሉም የተሻለ የመፍትሔ መንገድ መሆኑ ታይቷል በማለት አስገንዝቧል።

ስለዚህም ሲኖዶሱ መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት እንዲመለከተው በጠየቀው መሠረት፤ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሲኖዶሱ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሁሉ እንደሚያደርግ ይገልጻል ሲል አመልክቷል።