አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ35ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ አርሰናል ከበርንማውዝ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ ቀን 8 ሰዓት ከ30 በምሳ ሰዓት የጨዋታ መርሐ ግብር አስቶንቪላ ከፉልሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ቀን 11 ሰዓት ላይ ደግሞ ኤቨርተን ከኢፕስዊች ታውን እንዲሁም ከፕሪሚየር ሊጉ የተሰናበቱት ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝሃምፕተን ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም በርንማውዝን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
መድፈኞቹ የሁለተኛነት ደረጃቸውን አስጠብቀው ሊጉን ለመጨረስ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ትናንት በሜዳው ኢቲሃድ ስታዲየም ዎልቭስን ያስተናገደው ማንቼስተር ሲቲ 1 ለ 0 በማሸነፍ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 ዝቅ በማድረግ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በአቤል ንዋይ