አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 625 ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷በንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከ46 በመቶ ወደ 61 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች መመረታቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ገልጸው÷ንቅናቄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ የሚከፈተው 3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ እስካሁን በንቅናቄው የተገኙ ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን