የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አስገኝቷል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

By abel neway

May 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ለ5 ቀናት በሚቆየው የ2017 “ኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖ ከወትሮው በተለየ መልኩ በአጠቃላይ 288 ድርጀቶች ምርታቸውን ማቅረባቸው ተመላክቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው÷ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች አስገኝቷል፡፡

ለአብነትም ዓመታዊ የዘርፍ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው በ2016 ዓ.ም በ8 ነጥብ 4 በመቶ ያደገ ሲሆን÷ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በ12 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡

የኢንዱስትሪዎች የማምረት ዐቅም በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ ወደ 61 ነጥብ 2 በመቶ ሲያድግ፤ ገቢ ምርት በመተካት በ2014 በጀት ዓመት የነበረው 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ በ2017 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ወደ 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ማደጉ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ የማኑፋክቸሪንግ የኃይል ፍጆታ በ2015 ዓ.ም ከነበረበት 3 ነጥብ 88 ቢሊየን ኪሎዋት ሰዓት በ2016 ዓ.ም ወደ 4 ነጥብ 67 ቢሊየን ከፍ ማለቱ ተብራርቷል፡፡

የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የብሔራዊ አካውንት መረጃ እንደሚያሳየው÷ የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ እሴት ጭማሪ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ይሄም የማኑፋክቸሪንግ እሴት የተጨመረበት ምርት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገደማ በ2016 ዓ.ም ወደ 9 ነጥብ 25 ቢሊየን ዶላር ማደጉ ተመልክቷል፡፡

ይህ ከፍተኛ የሆነ እሴት ጭማሪ ከላይ የተጠቀሰውን ትክክለኛ የምርት ዕድገት የሚያንፀባርቅ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

በቀጣይ ዓመታት ለአግሮ ፐሮሰሲንግ መስፋፋት የሚያግዙ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ማሽኖችን፣ በገጠር የመስኖ እና የቤት ውሰጥ ኃይል አቅርቦት ችግሮችን የሚፈቱ የነጻ ኃይል ማምረቻ ማሽኖችን ለማምረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ፈጠራን ማበረታት እና አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ የማቅረብ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመርሐ ግብሩ ላይ ተነስቷል፡፡