አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ ዓመታት በገጠር የመስኖና የቤት ውስጥ ኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚፈቱ የነጻ ሃይል ማምረቻ ማሽኖችን አምርተን ተደራሽ እናደርጋልን ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው÷በዚህም ንቅናቄው ሥራ ያቆሙ ነባር ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ምርቶችን በአይነት፣ በጥራትና በመጠን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው÷ በዚህም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈው ወደ ውጪ ገበያ የመቅረብ ሒደት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ኤክስፖው ከወትሮው በተለየ የማምረቻ ማሳሪዎችን በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
በኤክስፖው አምራቾች ብረትን እንደሸማ ሰርተው ዓለም የደረሰበትን የጥራት ደረጃ በማሟላት ዘመናዊ ማሽኖችን ለዕይታ አቅርበዋል ብለዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ 288 ኢንዱስትሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸው÷ በዚህም ውጤታማ ግብይት ይፈፀማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡
መንግስት አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በወሰዳቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞችና ምቹ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር በተከናወነው ሥራ አበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል፡፡
አፈጻጸሙም ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ትልም የሚሳካበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያመላከተ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በንቅናቄው የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠልና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በቀጣይ ዓመታት ለአግሮፕሮሰሲንግ መስፋፋት የሚያግዙ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያዎችን በማምረት የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማስፋፋት ይሰራል ብለዋል፡፡
በተለይም በገጠር የመስኖና የቤት ውስጥ ኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግሮችን የሚፈቱ የነጻ ሃይል ማምረቻ ማሽኖችን አምርትን ተደራሽ እናደርጋልን ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ