የሀገር ውስጥ ዜና

የአርበኞች ቀን የቅኝ ግዛት እሳቤ በአፍሪካ ምድር መሸነፍ እንደሚችል ዳግም የተገለጠበት ነው- ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

By ዮሐንስ ደርበው

May 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርበኞች ቀን (የድል ቀን) የቅኝ ግዛት እሳቤ በአፍሪካ ምድር መሸነፍ እንደሚችል ዳግም የተገለጠበት ብርቱ የተጋድሎ መገለጫ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስገነዘቡ፡፡

84ኛው የጀግኖች አርበኞች የድል ቀን አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት ዐደባባይ ተከብሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ዕለቱ ለኢትዮጵያውያን ነፃነት ዋጋ ለከፈሉ በሙሉ ታላቁ ድል የሚዘከርበት ነው ብለዋል።

ዕለቱ የቅኝ ግዛት እሳቤ በአፍሪካ ምድር መሸነፍ እንደሚችል ዳግም የተገለጠበት ብርቱ የተጋድሎ መገለጫ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀኑን ኢትዮጵያን በሚመጥን ሁኔታ ማክበር እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በቁርጠኝነት የተመሙ አያሌ ኢትዮጵያውያን አሸናፊ የሆኑበት እንዲሁም ሀገርን አሳልፈው የሰጡ በሙሉ ተሸናፊነታቸው በተግባር የተገለጠበት ዕለት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሰላምና ነፃነትን ከሌላ የውጭ ኃይል የምንማረውና የምንቀበለው ሳይሆን፤ በራሳችን የነፃነት ብርቱ ፍላጎት የተመሠረተ መሆኑን ያረጋገጥንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጀግንነት ተጋድሎ ርኅራሄ ነበረው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ጀግኖች አርበኞች ጥንካሬን ከርኅራሄ ጋር በማዋሃዳቸው እጅ ለሰጡ በሙሉ አክብረው ይዘዋል ይህም ታላቁ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ነው ብለዋል፡፡

የስንፍና ፖለቲካን ለመረጡ ኃይሎች ጀግንነት በሰላሚዊ መንገድ የሚገለጥ በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሔኖክ ለሜ