የሀገር ውስጥ ዜና

ለጎንደር ከተማ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሀብት ለማሰባሰብ ውይይት እየተካሄደ ነው

By Abiy Getahun

May 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለጎንደር ከተማ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ሀብት ለማሰበሰብ ያለመ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በዚሁ ወቅት፤ ከተማዋን የተሻለች ለማድረግ ቀደም ሲል በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በርካቶች ተሳትፎ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ሌሎች ከተሞች ጎንደርን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸው፤ የከተማው ነዋሪና አመራርም ገቢ በማሰባሰብ አሻራቸውን ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ግርማይ ልጅዓለም በበኩላቸው፤ ጎንደርን ይበልጥ የቱሪስት መስኅብ በማድረግ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በኮሪደር ልማቱ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ቃል መገባቱን ጠቅሰው፤ ከ450 በላይ ተሳታፊዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

የከተማዋን የኮሪደር ልማት ሥራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በቀጣይ በጎንደር ከተማ በየተቋማቱ እና በክፍለ ከተሞች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሆነ ይታወቃል።

በሄለን እያዩ