አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የግብርና ስርዓቱን ለማዘመን የዘርፉ ባለሙያዎች ዲጂታል የልምድ ልውውጥ መድረኮች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የግብርና እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች አማካሪ የባለሙያዎች ቡድን ይፋዊ የምስረታ መርሐ ግብር በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት፥ የአማካሪ ቡድኑ መቋቋም በቀጣናው ግብርናን ለማዘመንና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከምግብ ዋስትናና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን የጋራ ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸው፥ በቀጣይ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራትና የአጋር ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፥ በቀጣናው በግብርና ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።
በኃይለማርያም ተገኝ