የሀገር ውስጥ ዜና

የዘመናችን አርበኝነት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By ዮሐንስ ደርበው

May 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘመናችን አርበኝነት የኢትዮጵያን የተሟላ ሉዓላዊነትና ብልፅግና ማረጋገጥ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደውን አራተኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር በይፋ አስጀምረዋል።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የዚህ ዘመን ትውልድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ድህነትና ኋላ ቀርነትን በማሸነፍ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች ሀገር የመገንባት ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የሀገራት የለውጥ ጉዞ የሚወሰነው በሀብት ብዛት ሳይሆን ሀብትን በመጠቀም መሆኑን በመጥቀስ፤ የሀገርን ሀብት በሚገባ ለመጠቀም ደግሞ ክህሎት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ፈጠራ እና የክህሎት ልማት ለኢትዮጵያ መዳኛዋ መሆኑን መንግሥት ተገንዝቦ ሀገራዊ አቅምን በመደመር እና ራሱን የቻለ ተቋም በማደራጀት ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት ግብርናን የሚያዘምኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ የተመቸ እና ውጤታማ የሚያደርጉ፣ ዲጂታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ ቴክኖሎጂዎችን እየፈጠሩ ብቁ ሙያተኞችንም እያፈሩ ነው ብለዋል።

በየዓመቱ የሚዘጋጁት የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ውድድሮች በፈጠራ የበሰሉ ብሩህ አዕምሮዎችን፣ የተፍታቱ እጆችን፣ በክህሎታቸው የበቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ መድረኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶች በፈጠራና ምርምር ሀገርን ወደ ብልጽግና እንዲያሸጋግሩ ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።