የሀገር ውስጥ ዜና

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከእስራኤል አቻቸው ጋር ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

May 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ከፍተኛ የንግድ ልዑካን ቡድን መርተው አዲስ አበባ ከገቡት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በዘርፉ የተሻለ ልምድ ካላት እስራኤል ጋር ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጌዲዮን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንዳመላከተው፤ ጠላታችን የሆነውን ሽብርተኝነት ለመዋጋትም ከእስራኤል ጋር ትብብራችንን እናጠናክራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጌዲዮን ሳር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋና መግቢያ በር በመሆኗ የእስራኤል ሁነኛ አጋር ነች ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ታሪካዊ እና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እስራኤል ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡

ሀገራቱ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት በሁለንተናዊ ዘርፎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በጤና፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ እና መሰል ዘርፎች በተሻለ ትብብር ለመሥራት ሚኒስትሮቹ መምከራቸው ተገልጿል፡፡