የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮ እስራኤል ቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ ነው

By Adimasu Aragawu

May 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና እስራኤል የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ፎረሙ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት እየተካሄደ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ እና እስራኤልን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ በኢትዮጵያ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ልዩ እና ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት በግብርና፣ በውሃ አስተዳደር፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ዘርፎች ላይ መስፋፋቱን ገልጸዋል።

መድረኩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደምትገኝም አመላክተዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር እስራኤል የኢትዮጵያ የስኬቷ አካል መሆን ትፈልጋለች ብለዋል።

ከልዑካኑ መካከል የተወሰኑት እዚሁ በኢትዮጵያ የተወለዱ መሆናቸውን አንስተው÷ የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ለኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸው መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን፣ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ሌሎች ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በእስራኤል በኩልም የትይዩ ተቋማት ልዑካን ቡድን አባላት የተገኙ ሲሆን÷ ፎረሙ የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል።

በአሸናፊ ሽብሩ