የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው

By Melaku Gedif

May 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለ2017/18 ምርት ዘመን ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ታከለ ቁሩንዴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የግብርና ግብዓት አቅርቦትን በተገቢ ሁኔታ ማሳለጥ ይገባል፡፡

በመኸር እርሻ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ የምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦትን ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው÷በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይም ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተሰብስቦ ለአርሶ አደሩ በመሰራጨት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የበቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ እና የሌሎች ሰብሎችን ምርጥ ዘር በፍጥነት ለማሰራጨት ከዩኒየኖችና እና ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም ቅድሚያ ለሚዘራው የበቆሎ ሰብል ከ139 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ