አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማቅረብና በመተግበር የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 24ኛው የጋራ ፎረም ጉባዔ በወሎ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባዔው ላይ በ”ቨርቹዋል” ንግግር ያደረጉ አቶ አረጋ ከበደ ÷ ዩኒቨርሲቲዎች የማሕበረሰብን የእድገት ደረጃ በመቃኘት አጋዥ ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልልን ኢኮኖሚ እድገት ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመው ÷ይህም ክልሉ ከገባበት ዘርፍ ብዙ ቀውስ እንዲወጣ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የመልማት ጸጋን መሠረት ባደረገ መልኩ ስድስት የልማት ኮሪደሮች መለየታቸውን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡
ስለሆነም ዩኒቨርሲቲዎች ይህን ባገናዘበ መልኩ በጥናት፣ በምርምር እና በማማከር አገልግሎት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
ክልሉ ካጋጠመው ማህበራዊ ቀውስ እና ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲወጣ ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር የታገዘ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ ረገድ የክልሉ መንግስት ለዩኒቨርሲቲዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡