የሀገር ውስጥ ዜና

ገዢ ትርክትን ለማስረጽና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የቋንቋ ልማት ላይ መስራት ይገባል- ሚኒስቴሩ

By Mikias Ayele

May 06, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ገዢ ትርክትን ለማስረጽ እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የቋንቋ ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

“የብዝሃ ቋንቋ ልማት ለሕብረ ብሔራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሃሳብ የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡

መድረኩ ብዝሃ ባህልና ቋንቋን ለማልማት ሕገ መንግስታዊ መርሆዎችንና መብቶችን ተከትሎ በለውጡ መንግስት የተዘጋጀውን የቋንቋ ፖሊሲ ተግባራዊነት ለማሳለጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የሕብረተሰቡን ቋንቋ መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም ባህሉንና ማህበረሰባዊ እውቀቶቹን ከማሳደግ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ብዝሃ ባህል ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ ገዢ ትርክትን ለማስረጽና ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን ለመገንባት የቋንቋ ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አምስት ቀንቋዎችን የፌደራል መንግስት የሥራ ቋንቋ የማድረግ ሒደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሚኒስትሯ÷እስካሁን የአምስት ቋንቋዎች መመሪያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የብዝሃ ቋንቋ ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ አጠቃቀም ሥነ-ምግባር መመሪያ፣ የምልክት ቋንቋ ስትራቴጂና የትርጉም ሙያ የብቃት ማረጋገጫ መመሪያ መዘጋጀቱ እንደ ትልቅ ስኬት የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቋንቋ ለማልማትና ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል፡፡

የቋንቋ ፖሊሲውን  ትግበራ ሒደት ማሳለጥ የሚያስችል በአምስት የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የቋንቋ ፍኖተ ካርታ መመሪያ መጽሐፍ በመድረኩ መመረቁም ተመላክቷል፡፡

በሚኪያስ አየለ