ቢዝነስ

የእንሥሣት ወጪ ንግድን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

May 08, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የእንሥሣት ወጪ ንግድን ለማሳደግ የምታከናውነው ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ በመንግስት የተወሰዱ ርምጃዎች በዘርፉ ያለውን ተጠቃሚነት እያሳደገ መጥቷል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እንሥሣቶች በጎረቤት ሀገራት ስም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ምርት ለውጭ ገበያ በስፋት ማምረት የተቻለበት ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከእንሥሣት ወጪ ንግድ 128 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።

ይህ ውጤት ትልቅ ለውጥ እንደሆነ በመግለጽ በአፋር ክልል ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው ሚሌ ኳራንቲን ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

እንሥሣቱ ወደ ሚሌ ኳራንቲን ገብተው የኢትዮጵያን ሥም በመያዝ ለውጭ ገበያ እየቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል።

የእንሥሣት ሀብት ትልቅ የውጪ ምንዛሬ የሚገኝበት በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ የተለያዩ መስረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የኳራንቲን ማዕከላትን የማስፋት ሥራዎች በድሬዳዋ፣ ጂግጂጋ እና ቦረና እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የአፋር ክልል የእንሥሣትና ዓሣ ሃብት ቢሮ ሃላፊ ኢብራሂም መሐመድ በበኩላቸው፤ ክልሉ በዚህ ዓመት ብቻ በሚሌ ኳራንቲን በኩል 480 ሺህ እንስሳት ወደ ውጪ እንዲላክ ማድረጉን ተናግረዋል።

ወደ 18 የሚሆኑ ለእንስሳቱ አስፈላጊ የሆኑ መኖ፣ ውሃ እና ማቆያ ያላቸው የአካባቢ ገበያዎች መመስረታቸውንም ጠቁመዋል።

በዮናስ ጌትነት