አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከባህል ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ስብራትን ለመጠገን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ተሀድሶ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠና መድረኩ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ደራራ ከተማ÷ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ያጋጠሙ የባህል ስብራቶችን ለመጠገን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የባህል እድሳት ሲባል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ቴክኖሎጂያዊ ጉዳዮችን በውስጡ ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው÷ የባህል እና እሴት ስብራቶችን ለመቅረፍና ወደ ቀደመው ቦታ ለመመለስ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተከሰተው የባህል ስብራት በዜጎች መካከል ባለው የመከባበር እና የመተሳሰብ እሴት ላይ ጫና በመፍጠሩ ብልሹ አሰራር እና ሌብነት እንዲፈጠር ስለማድረጉ በአብነት ተነስቷል።
በመሆኑም ያጋጠሙትን የባህል ስብራቶችን ለመጠገን የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የድርሻቸውን ለመወጣት መስራት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
በአቤል ንዋይ